ሱናሕ፡-ሁለተኛው የሸሪዓ ሕግ ምንጭ
Keywords:
ሱናሕ, ሀዲስ, ሸሪዓ, ምንጭነት, አስረጂነት, ተዓማኒት, ምዘና, የሕግ ብዝኃነትAbstract
Sharia courts have been functioning in Ethiopia for more than half a century, since before the imperial regime; facing the challenges of time, they still exist and operate at different levels across the country on the basis of what has been reaffirmed under the FDRE Constitution. This has resulted in what is known as legal pluralism making Sharia Courts the only system of dispute resolution operating beside the regular judicial system of the country. It is provided in the Federal Consolidation Proclamation No. 188/1999 Article 6(1) that Sharia courts apply Islamic law to disputes arising from personal and family matters falling under their jurisdiction upon the consent of the parties; and the primary source of Islamic law is to be found in the Quran and the Sunnah. This paper delves into the second source of Sharia i.e. the Sunnah which represents the practice and teachings of Prophet Muhammad. Two kinds of Sunnah have been identified by Sharia jurists. The first is what is termed as legal Sunnah containing the principles and rules of conduct that Muhammad taught in his prophetic capacity; whereas the other type of Sunnah which is non-legal refers to those sets of practices that Muhammad has followed as a matter of his personal choice, or reflecting the societal culture of his Arab society of the time; added to non-legal Sunnah is the decisions and measures that Muhammad has taken in his status as leader and judge for the political and judicial matters of the Muslim community of that time. It is authoritatively held that Non-legal Sunnah is not binding and not applicable directly and automatically to cases arising Muslim communities that came after until the present time without passing through contextual scrutiny by authorized organs. This dual look at the prophetic legacy of Sunnah indicates to fact that oral traditions through which the Sunnah was reported do not make differentiation of these two set of groups of the Sunnah from Sharia perspective. As the Sunnah has come down through reports called Hadith, the reliability of the latter is a big issue in Islamic scientific discourses; and a separate discipline is devoted for the authentication of prophetic traditions; this field of Islamic study viz. Usul al-Hadith, embraces a scheme for the authentication of Hadith traditions that can generally be categorized as chain-based (Isnad) and content-based (Matn). Once a particular report passes these two-step tests of authenticity and acceptability, it can safely be utilized as a source of Sharia representing the actual prophetic Sunnah. Proper understanding in the nature and characteristics of Sunnah as source of Sharia and the reliability of the Hadith reports before basing Sharia rulings on Sunnah is necessary for Sharia courts operating in Ethiopia and anywhere else across the global Muslim community.
አሕጽሮተ-ጥናት
የኢትዮጵያ ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች (ፍ/ቤቶች) ከኃይለ-ሥላሴ ዘመነ-መንግሥት በፊት ጀምሮ በሥራ ላይ የነበሩ ሲሆን፣ ግማሽ ምዕተ-ዓመታትን ተሻግረው፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገመንግሥት የተሰጣቸውን የአቋም ማጠናከሪያ ተንተርሰው፣ በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት ደረጃ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ጠቅላይ ፍ/ቤት ተደራጅተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ እውነታ፣ ከሕግ እውቅና ውጪ ካለው የሕግ ብዝኃነት ሌላ ሕጋዊ መሠረት ባለው የብዝኃነት መድረክ ላይ ከመደበኛው የፍ/ቤት ሥርዓት በተጓዳኝ በመስራት ላይ ያለ ብቸኛ የዳኝነት ሥርዓት ያደርገዋል፡፡ በሸሪዓ ፍ/ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ ቁጥር 188/1992 አንቀጽ 6(1) መሠረት፣ ሸሪዓ ፍ/ቤቶች በባለጉዳዮች ፈቃድ የሚቀርቡላቸውን የግልና የቤተሰብ ክርክሮች ለመዳኘት ተፈጻሚ የሚያደርጉት ሕግ ሸሪዓ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ በሸሪዓ ሕግ የምንጮች ተዋረድ ደግሞ፣ ከቅዱስ-ቁርአን ቀጥሎ፣ ሁለተኛ የምንጭነት እርከን ላይ የሚገኘው ሱናሕ ነው፡፡ ሱናሕ፣ ከቁርአን በተጓዳኝ፣ ከመጀመሪያው የሙስሊም ሕብረተሰብ በሥነ-ቃላዊ ዘገባዎች (አሃዲስ) አማካይነት ተላልፎ ወደ እኛ የደረሰውን የነቢዩ ሙሀመድ አስተምህሮትን የሚወክል፣ ነቢያዊ ፈለግ ወይም አሻራ ነው፡፡ ሱናሕ በሕግ ምንጭነቱ፣ ከቁርአን አንጻር ሲታይ፣ መጠነ-ሰፊ ሸሪዓዊ የሕግ ማዕቀፍ ያለው ሲሆን፣ ዘርፈ-ብዙ ግለሰባዊና ማሕበረሰባዊ ግንኙነቶችን የሕግ መርሆዎችንና ልዩ ድንጋጌዎችን አቅፎ ይዟል፡፡ ሱናሕን የሸሪዓ ምንጭና አስረጂ አድረጎ በመጠቀም ረገድ፣ መሠረታዊ የሆኑ የሕግነትና የተዓማኒት ጭብጦች ይነሳሉ፡፡ ከሕግነት ባህርይ አኳያ፣ ሱናሕ፣ ደንጋጊ እና ኢ-ደንጋጊ በተሰኙ ሁለት ክፍሎች የሚታይ ሲሆን፣ ደንጋጊ ሱናዎች፣ ሙሀመድ በነቢይነት ደረጃችው መለኮታዊ ተልዕኮ ተላብሰው ያስተላለፏቸውን የሕግ መርሆዎችና ድንጋጌዎችን የሚይዝ ሲሆን፣ ኢ-ደንጋጊ ሱናሕ ደግሞ ሙሀመድ እንደ ግለሰብ፣ ግላዊ ምርጫቸውንና ባህላቸውን ተከትለው የፈጸሟቸው ተግባራትን፣ እንደ አመራርና ዳኛ በተለያዩ አጋጣሚዎች የወሰዷቸውን እርምጃዎችና ውሳኔዎችን የሚመለከት ሲሆን፣ ይህ የሱናሕ ክፍል ለሸሪዓ ምንጭነት ቀጥተኛ የሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ይህ የሱናሕ ሁለትዮሽ አተያይ፣ ነቢያዊ ፈለግ የተላለፈባቸው ዘገባዎች፣ በሙሀመድ ግለሰባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ነቢያዊ እና የዳኝነት ደረጃዎች መካከል ልዩነት የማያደርግ የሥነ-ጽኁፍ አሻራ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ሱናሕ የተላለፈው በሥነ-ቃላዊ ዘገባ (ሀዲስ) አማካይነት በመሆኑ፣ የዘገባ ተዓማኒት ጥያቄ አይቀሬ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ፣ በሀዲስ ምዘና ሥርዓት ጥናት (ኡሱል አል-ሀዲስ) በዳበረው መሠረት፣ ዘገባዎች ነቢያዊ ሱናሕ ያዘሉ ለመሆናቸው በቅድሚያ የዘገባ ተዓማኒነታቸው (ኢስናድ) እና የይዘት (መትን) ቅቡልነታቸው ሊፈተሸ ይገባል፡፡ አንድ የሀዲስ ዘገባ እነዚህን ሁለት የኢስናድ እና የመትን ምዘና እርከኖች ካለፈ፣ ነቢያዊ ሱናሕን የሚወክል ዘገባ መሆኑ ተረጋግጦ አስተማማኝ የሸሪዓ ምንጭ በመሆን ጥቅም ላይ ሱናሕ…
ሊውል ይችላል፡፡ ሸሪዓ የኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት አካል እና በሸሪዓ ፍ/ቤቶች አማካይነት ገቢራዊ የሚደረግ እንደመሆኑ፣ ለዳኝነት ለሚቀርቡ የግልና የቤተሰብ ጉዳዮች ሸሪዓዊ እልባት በመስጠት ረገድ፣ የሕግነት ባህሪያላቸው ሱናዎችን ከሌላቸው፣ ተዓማኒ የሆኑትን ካልሆኑት ለመለየት፣ በዚህ ጽኁፍ ተጠቃለው የቀረቡትን፣ እንዲሁም በሸሪዓ መሠረተ-ሐሳቦች ጥናት ዘርፍ (ኡሱል አል-ፊቅሕ) እና የሀዲስ ምዘና ሥርዓት ጥናት በሥፋትና በጥልቀት የዳበሩትን የሱናሕ እና የሀዲስ የመርሆ እና የምዘና ሐሳቦችን መረዳት፣ በሃገራችን ትክክለኛ የሸሪዓ አረዳድና አፈጻጸም እንዲሰፍን በማድረግ ሂደት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡